አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሐረሪ ክልል የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት የመንግስት እና የፓርቲ እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷መድረኩ ባለፉት 6 ወራት የተሰሩ የመንግስትና የፓርቲ ሥራዎች ተገምግመው ለቀጣይ ጊዜ ዝግጅት የሚደረግበት ነው ብለዋል።
በግምገማው በአንደኛው ሩብ ዓመት በተካሄዱ ግምገማዎች በየዘርፉ የተሰጡ ግብረ መልሶችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች ተፈጻሚ መደረጋቸው ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አንስተዋል፡፡
በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ፣ መልካም አስተዳደር፣ ገቢ አሰባሰብ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ሕገ ወጥ ንግድ እና ሌሎች ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ገልፀዋል።
በኢኮኖሚ ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ባስመዘገቡት የኢኮኖሚ ዕድገትና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ባደረጉት ልክ እንደሚገመገሙ ጠቁመዋል፡፡
ሃላፊነታቸውን በተገቢ ሁኔታ ባልተወጡ አመራሮች ላይ የግምገማውን ውጤት መሰረት በማድረግ ርምጃ እንደሚወሰድ ማሳሰባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡