Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው – የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅና ሊደገፍ የሚገባው ነው ሲሉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ የካናዳ፣ ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ቤልጅዬም፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ እና ሉክዘምበርግ አምባሳደሮች በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን ጎብኝተዋል፡፡

አምባሳደሮቹ በዚህ ወቅት÷ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ስደተኞችን ተቀብላ በሰላም እንዲኖሩ የጎላ አስተዋፅኦ በማበርከቷ አመስግነዋል፡፡

የየሀገራቱ መንግስታት ከዚህ ቀደም የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ እንደነበር ጠቅሰው÷ በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀብላ በማስተናገድ እያሳየች ያለው ቁርጠኝነት የሚደነቅና ሊደገፍ የሚገባው ነው ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሐሰን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን ተቀብላ ከምታስተናግድባቸው ክልሎች መካከል ከፍተኛ የስደተኛ ቁጥር የሚገኘው በጋምቤላ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ለስደተኞቹ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልጸው÷በጋምቤላ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት አገልገሎት እያገኙና ሰብዓዊ ድጋፍና ጥበቃም እየተደረገላቸው መሆኑን አንስተዋል።

በዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ለስደተኞቹ የሚሰጠው እገዛና ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ረገድ የሀገራት አምባሳደሮች በመጠለያ ጣቢያዎች በመገኘት ያደረጉት ጉብኝት ትልቅ ትርጉም እንዳለው አውስተዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ÷የክልሉ መንግስት በርካታ ስደተኞችን በመቀበል መጠለያን ጨምሮ ያለውን ውስን ሃብት በማጋራት ጭምር ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ለስደተኞች የሚደረገው ጥበቃና ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው÷ ባለድርሻ አካላት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

Exit mobile version