Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ህገወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለመከላከልና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት መስራት ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ህገወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለመከላከልና ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በተለየ ትኩረት መስራት እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ አሳሰቡ።

ብሔራዊና ክልላዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረቶች የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ የተገኙት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ÷ ህጋዊ ፍልሰት ለማጎልበት የተሰሩ ሥራዎች ውጤት እያስመዘገቡ ቢሆንም በህገወጥ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎች ለሁለንተናዊ ችግር እየተጋለጡ እና ሁኔታውም አሳሳቢ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከ1 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች እንደሚገኙም ነው የገለጹት፡፡

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ በበኩላቸው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት አሳሳቢ ስለሆነ የወንጀል ሰለባ የሚሆኑ ወገኖችን ለመታደግ በልዩ ትኩረት መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት።

ችግሩን ለመቀልበስ በተግባር የሚገለጥ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን ማሳየት ይገባልም ብለዋል።

ህገወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለመከላከል ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር የሚያሻግሩ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር እንዲሁም የዜጎች መብትና ደህንነት የተረጋገጠበት መደበኛ ፍልሰትን ለማጎልበት ብሔራዊ ምክር ቤት ተቋቁሞ እየተሰራ ስለመሆኑም ተገልጿል።

በዙፋን ካሳሁን እና ታሪኩ ለገሰ

Exit mobile version