አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማዎች ወይንም ሊቃውንቶች የሦስተኛ ዓመት መደበኛ ጉባዔውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።
ጉባዔው የሁለት ቀናት ቆይታ ሲኖረው፥ በተለያዩ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ጉዳዮች ላይ በስፋት ይመክራል ተብሏል።
በጉባዔው የቀረቡ ሪፖርቶችን ገምግሞ ካፀደቀ በኋላ የቀጣይ ስድስት ወራት ዕቅድ እና በጉባዔው ለታቀዱ ተግባራት ማስፈፀሚያ የሚሆን በጀት ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በጉባዔው ላይ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ ዑለማዎች፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የዑለማዎች ጉባዔ ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋን ጨምሮ የክልል መጅሊስ አመራሮች ተገኝተዋል።
ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ ዑለማዎች አበክረው መስራት ይገባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።
ጉባኤው በታላቁ ረመዳን ወር ዋዜማ ላይ የሚካሄድ መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው አንስተው፤ እንደ ወትሮው ሁሉ ወሩን በመተጋገዝና በአብሮነት ሕዝበ ሙስሊሙ ሊያሳልፈው ይገባል ብለዋል።
በመራኦል ከድር