አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፍትሕ ሚኒስትር ሀና አርአያሥላሴ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ውይይቱ የተደረገው በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ ከሚገኘው 58ኛው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የከፍተኛ ደረጃ መድረክ ጎን ለጎን መሆኑ ተገልጿል፡፡
በውይይቱ ላይም ኢትዮጵያ ከወራት በፊት ባቀረበችው የሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ግምገማ መድረክ ሀገራዊ ሪፖርት ዝግጅት ኮሚሽኑ ላደረገው ድጋፍ ሚኒስትሯ አመሥግነዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመድረኩ 316 ምክረ ሀሳቦች እንደተሰጧት አውስተው፤ በቀጣይ ምክረ ሀሳቦቹን ለመተግበር የከፍተኛ ኮሚሽነሩ ጽሕፈት ቤት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
መንግስት ያለፉትን በደሎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ፤ እንዲሁም መሰረታዊ ልዩነቶችን በሀገራዊ ምክክር እልባት ለመስጠት እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠሉንም አስረድተዋል፡፡
ነጻ እና ገለልተኛ የሽግግር ፍትሕ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችም እየተዘጋጁ ነው ማለታቸውን የፍትሕ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ኮሚሽነሩ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በሁሉን አቀፍ ሰብዓዊ መብት ግምገማው ላይ በተሰጧት ምክረ ሀሳቦች ትግበራ ላይ ጽሕፈት ቤታቸው እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡