Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኬንያ አሸባሪው የሸኔ ቡድንን እያጸዳች መሆኑ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኬንያ ብሔራዊ የፖሊስ አገልግሎት በግዛቱ የመሸገውን የሸኔ የሽብር ቡድን የማጽዳት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገለጸ።

‘ኦንዶአ ጃንጊሊ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ተልዕኮ፤ በማርሳቤት እና ኢሲዮሎ ግዛቶች የሚገኙ፣ በኬንያ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥሩ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል።

በኬንያ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ታጣቂ ቡድኑ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ጠረፍ አካባቢዎች እያከናወናቸው ያሉትን ሕገ-ወጥ ተግባራት ለመከላከል የጸጥታ አካላት ርምጃ እየወሰዱ መሆኑም ተገልጿል።

በዚህም የአደንዛዥ እጽ ቁጥጥር እና የመሳሪያ ዝውውር ቁጥጥር ዩኒት በማቋቋም ርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ አስታውቋል።

እስከአሁንም ቡድኑ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ ዶክመንቶች፣ መሳሪያዎች እና የተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን ለመስራት የሚውሉ ቁሳቁሶች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የሰራዊቱ መሪዎች መጠቀሚያ ናቸው የተባሉ መኪናዎች፣ ሞተር ሳይክሎች፣ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና በርካታ ገንዘቦች መያዛቸው ነው የተነገረው።

በቀጣይም የኬንያ መንግስት በቀጣናው ዘላቂ መረጋጋትን ለማስፈን የመልሶ ማቋቋም እና የረዥም ጊዜ የጸጥታ ስትራቴጂ ላይ እንደሚያተኩር መገለጹን ኬቲኤን ኒውስ ኬንያ ዘግቧል።

የሸኔ ታጣቂ ቡድን ይጠቀምባቸው የነበሩ 14 ካምፖችን ማውደሙን የገለጸው ፖሊስ፤ ለስልጠና፣ ለአደንዛዥ እጾች መስሪያ እና ለፕሮፓጋንዳ ማዕከልነት ሲጠቀምባቸው የነበሩት ቦታዎች ከጥቅም ውጪ መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያና የኬንያ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ በሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን ማካሄድ መጀመራቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል።

በሔለን ታደሰ

Exit mobile version