Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአጀንዳ ባልተሰባሰበባቸው አካባቢዎች አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ የህዝቡ ሚና ወሳኝ ነው – መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግጭት በሚታይባቸው አካባቢዎች ለምክክር ሂደቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የህዝቡ ሚና ወሳኝ መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ‘አንድ ጉዳይ’ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት አመታት ባከናወናቸው ተግባራትና ቀጣይ እቅዶቹ ዙሪያ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

የአማራና ትግራይ ክልሎችን ጨምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ባልተከነወነባቸው አካባቢዎች ለምክክር ሂደቱ አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ የህዝቡ ሚና ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የምክክር አስፈላጊነት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፤ ህዝቡ ባለፉት ጊዜያት ከደረሱ ጥፋቶች በመማር ግጭት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ለማምጣት ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡

በሌሎች ሀገራት የመንግስትና የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የምክክር ሂደቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ እክል መፍጠራቸውን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጣልቃ ገብነትን እንደማይፈቅድ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

የምክክር ኮሚሽኑን ስራዎች የመምራት ፍላጎት ያሳዩ የውጭ አካላት እንደነበሩ አስታውሰው፤ ሆኖም በፋይናንስ እገዛ ከማድረግ ባለፈ ጣልቃ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቀሪ ስራዎችን እንዲያጠናቅቅ የስራ ዘመኑ በአንድ አመት መራዘሙጠቅሰው፤ በቀጣይ ኮሚሽኑን የማጠናከር ስራዎች በትኩረት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከ1 ሺህ 100 በላይ ወረዳዎችን ተደራሽ ማድረጉን ገልጸው፤ በሺዎች የሚቆጠሩ አጀንዳዎች በተለያዩ መንገዶች ለኮሚሽኑ መቅረቡንም ገልጸዋል፡፡

የታጠቁ ሀይሎችን በድርድር ለመመለስ የተጀመረው ጥረት የሰላም በርን ለመክፈት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የተናገሩት መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)፤ የአንድን ሀገር ችግር ከመሰረቱ መቅረፍ የሚቻለዉ በድርድር በመሆኑ የድርድር ባህላችንን ማዳበር እና የተጀመሩ ጥረቶችን ማጠናከር ይገባናል ብለዋል።

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በተደረገው የሰላም ስምምነት በርካታ ለውጦች መምጣታቸዉንም አንስተዋል።

በሃይለማርያም ተገኝ እና መቅደስ ከበደ

Exit mobile version