Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

 በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእጅ በእጅ ሽያጭ ደረሰኝ ወደ ግብይት ስርዓቱ ለማስገባት እየተሰራ ነው 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ማጭበርበርን የሚቀንስ እና በቀላሉ የሚለይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእጅ በእጅ ሽያጭ ደረሰኝ ወደ ግብይት ስርዓቱ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የታክስ ስርዓት ማጣጣምና የክልሎች ድጋፍ ዳይሬክተር ብርሃኑ አበበ፤ ደረሰኝ በአግባቡ ተይዞ ካልተሰራበት የገቢ አሰባሰቡ ላይ ከፍ ያለ ተፅዕኖ ያስከትላል ብለዋል።

አሁን ላይ ሚስጥራዊ ኮድ (QR CODE) ያለው ደረሰኝ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሀላፊነት ወስዶ እያተመ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም የ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ጥራዝ የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ ለድርጅቱ መቅረቡን ጠቁመዋል።

ልዩ መለያ ኮድ የተካተተበት የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ ማቅረቢያ ቀን የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅና አስታውሰው፤ ግብር ከፋዮች ሳይዘናጉ የደረሰኝ ህትመት ጥያቄ  እንዲያቀርቡ አስገንዝበዋል።

37 ሺህ ጥራዝ ደረሰኝ ታትሞ ለግብር ከፋዮች መሰራጨቱን ጠቅሰው፤ ደረሰኝ የደረሳቸው ግብር ከፋዮች አሮጌውን ደረሰኝ በማስወገድ በአዲሱ ብቻ መጠቀም እንዳለባቸው አመላክተዋል።

አዲሱ ደረሰኝ ያልደረሳቸው ግብር ከፋዮች ደግሞ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በነባሩ ደረሰኝ እንዲጠቀሙና ከሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ ግብይት በአዲሱ ደረሰኝ ብቻ ማከናወን እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በቀን 5 ሺህ ጥራዝ ደረሰኝ እያተመ የሚገኘው ድርጅቱ፤ ተጨማሪ ማሽን አስገብቶ እንዲሰራ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።

ደረሰኙ በፍጥነት ታትሞ ለግብር ከፋዮች እንዲደርስ ህትመት ለማከናወን አቅሙና ቴክኖሎጂው ያለው ተቋም መሳተፍ እንደሚችልም አመልክተዋል።

የደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች አዲሱን ደረሰኝ ማሳተምና የመጠቀም ግዴታ እንዳለባቸው ጠቁመው፤ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ግን ባይገደዱም መጠቀም ይችላሉ ነው ያሉት።

ከሐምሌ ጀምሮ አዲሱን ደረሰኝ በማይጠቀሙ ግብር ከፋዮች ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ እንደሚወሰድም ጠቁመዋል።

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version