Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሚኒስቴሩ የአፈር ማዳበሪያ ከክረምት በፊት ተጓጉዞ እንዲጠናቀቅ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፈር ማዳበሪያ የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊት በፍጥነት ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደሮች እንዲሰራጭ የሚከናወነው ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ጅቡቲ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሎጂስቲክስ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ መክረዋል፡፡

በውይይታቸውም በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚመራው የአፈር ማዳበሪያ ኦፕሬሽን ኮሚቴ እያከናወነ ያለውን ሥራ አድንቀዋል፡፡

ኮሚቴው በቅንጅት በመስራቱ በአንድ ቀን ከ18 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት መቻሉን ጠቅሰው÷የሎጂስቲክስ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

በኢትዮ-ጂቡቲ ኮሪደር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ እንደሆነ መግለጻቸውንም በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version