Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

 ወደ ተሟላ የግብርና ሥራ ለመግባት የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የጎላ ሚና አለው- አቶ አወል አርባ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሙሉ ዐቅም ወደ ግብርና ሥራ ለመግባት የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ ገለፁ፡፡

የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ሠነድ ላይ የማስተዋወቂያ መድረክ ተካሂዷል፡፡

አቶ አወል በመድረኩ ላይ ግብርና የዕድገት መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፤ በሙሉ ዐቅም ወደ ሥራ ለመግባትም የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

አመራሮች፣ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላትም ፖሊሲው የታለመለትን ውጤት እንዲያስገኝ እንዲረባረቡ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የግብርና ሜካናይዜሽንና ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ግብርናውን ካለበት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ይገባል ብለዋል፡፡

አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችንና የግሉን ዘርፍ በመደገፍ፤ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገትን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የተሻሻለው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ፤ የግብርናና ገጠር ልማት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ እና የግብርናውን ዘርፍ ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር የበለጠ ለማስተሣሠር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል፡፡

ፖሊሲው የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅና በዘላቂነት ለመጠቀም፣ ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ፣ የገጠር መዋቅራዊ ሽግግርን ለማሳካት ብሎም ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በአሊ ሹምባኽሪ

Exit mobile version