አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለ129ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቆ ወደ ሥራ መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።
129ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው የዓድዋ ድል መታሰቢያ እንደሚከበር ተገልጿል፡፡
በዚሁ ዕለት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳያጋጥም እና አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት፡-
• በቸርችል ጎዳና በቴዎድሮስ አደባባይ ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚወስደው መንገድ ባንኮ ዲሮማ መብራት
• ከአራት ኪሎ በራስ መኮንን ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚወስደው መንገድ ራስ መኮንን ድልድይ
• ከመነን አካባቢ እና የካቲት 12 ሆስፒታል በአፍንጮ በር ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚወስደው መንገድ አፍንጮ በር
• ከእሪ በከንቱ በኤሌክትሪክ ህንፃ ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚወስደው መንገድ ደጎል አደባባይ
• ከአዲሱ ገበያ በሰሜን ሆቴል ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚወስደው መንገድ ሰሜን መብራት
• ከመርካቶ በአቡነ ጴጥሮስ ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚወስደው መንገድ ደጃዝማች ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ
• ከእንቁላል ፋብሪካ በቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን ወደ ዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ዮሐንስ መብራት የሚወስዱት መንገዶች ከየካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ሠዓት ድረስ ለተሽከርካሪ ዝግ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡
ስለሆነም አሽከርካሪዎች ይህንን ተገንዝበው አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙና የትራፊክ ፖሊሶች የሚጠቁሟቸውን አማራጭ አቅጣጫዎችን በመጠቀም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ሕብረተሰቡም ማንኛውም አጠራጣሪ ጉዳይ ሲያጋጥመው በ0111110111 ወይም በነፃ ስልክ መስመር 991 በመጠቀም ለፖሊስ ማሳወቅ እንደሚችል የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።

