Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

 የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት ብሔራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ ይከናወናል- ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደት ብሔራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ ለማከናወን በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

ለዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት በፈረንጆቹ መጋቢት 19 ቀን 2025 ለሚደረገው 5ኛ ዙር የሥራ ቡድን ስብሰባ በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ ላለፉት 3 ቀናት ሰፊ ዝግጅት ሲደርግ መቆየቱን ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ከትናንት ጀምሮ ደግሞ የብሔራዊ ተደራዳሪ ኮሚቴ አባላት የቴክኒክ ኮሚቴው ዝግጅት ሥራ በቢሾፍቱ እየተገመገመ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡

የድርድሩን ባህሪና ውስብስብነት ያገናዘበ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ የጠራ አቋም መያዝ የሚያስችል ጥልቅ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በድርድሩ ምላሽ በሚሰጥባቸው ጉዳዮች በተለይም ከንግድና ንግድ ነክ ሕጎች፣ ለንግድ ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ ቴክኒካል ጉዳዮች፣ መመዘኛዎች፣ የወጪ ንግድ ፈቃድ፣ ከኢንቨስትመንት ማዕቀፍ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች አስተዳደርና አሰራር፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና አስተዳደር ጉዳዮች፣ ከግብር ጋር የሚያያዙ የተለያዩ የአግልግሎት ክፍያዎች እና ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች በመካሄድ ላይ ናቸው ብለዋል።

የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን የማሳካት ጉዳይና ሒደቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ጠንካራ አቋም መያዙንም አስገንዝበዋል፡፡

Exit mobile version