አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓልን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በመልዕክታቸው÷ የዓድዋ ድል የሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችን እና የጀግንነታችን ማሳያ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ÷ የዓድዋ ድል ጀግኖች አያት ቅደመ አያቶቻችን በአልሸነፍ ባይነት ተጋድሎ ያጎናፀፉን ፤ የፅናትና የአልበገር ባይነት ተምሳሌት መሆኑን አውስተዋል፡፡
ዓድዋ ኢትዮጵያዊያን ስለ ሀገር ክብርና ሉዓላዊነት በላቀ የሀገር ፍቅር፣ በቃላት በማይገለጽ ወኔና ጀግንነት ከጫፍ ጫፍ በመትመም ዘመናዊ ትጥቅ ታጥቆ የመጣን ወራሪ ሃይል ድል ያደረጉበት የጋራ አኩሪ ታሪክ፤ የብሔራዊ ክብራችን ዓርማ ነው ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራትና የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል የሆነው የዓድዋ ድል÷ የአልሸነፍ ባይነት መንፈስን አጎናፅፎ የመብትና የሉዓላዊነት ትግልን ያቀጣጠለ የመላው ጥቁር ህዝቦች የጋራ ታሪክ ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
የዛሬው ትውልድም የአንድነትን ሃያልነት ከጀግኖች አባቶቻችን በመማር፣ ከነጠላ ከፋፋይ ትርክቶች ይልቅ በገዢ ትርክት ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን በማፅናት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የራሱን አሻራ ሊያኖር ይገባል ነው ያሉት፡፡
ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው÷ ታላቁ የዓድዋ ድል የሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንና የጀግንነታችን ማሳያ፤ የክብርና የኩራታችን ምንጭ ብቻ ሳይሆን፤ የዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ተምሳሌት እና የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ መሰረት ጭምር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እኛ የዛሬ ዘመን ኢትዮጵያውያን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት በስኬት እየገነባን ዳግማዊ ዓድዋን በማስመዝገብ ላይ እንገኛለን ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይም ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን ጠብቀን በጋራ ጥረትና ትጋት የሀገራችንን የብልፅግና ከፍታ ዕውን በማድረግ ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ ድል እንደምናስመዘግብ የፀና ዕምነት አለኝ ብለዋል፡፡
ዓድዋን እንዘክራለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ኢትዮጵያን አጽንተን እናሻግራለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል በመልዕክታቸው፡፡
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ÷ዓድዋ የጀግንነታችን ጥግ፣ የኢትዮጵያዊነታችን ክብር ፣ የማንነታችን ጥንካሬ ተምሳሌት፣ የጥቁር ህዝቦች ኩራትና ድምቀት በመሆኑ ለኛ ኢትዮጵያውያን ክብራችን ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡
የዓድዋ ጦርነት የጣሊያንን ቅኝ ግዛት ፓሊስ ያኮላሸንበት፤ መላው ኢትዮጵያዊያን ለሀገራችን ሉዓላዊነትና ክብር ቅንጣት ያህል የማንደራደር ታላቅና ጀግና ህዝብ መሆናችንን ለዓለም ሕዝብ ያስመሰከርንበት ነው ብለዋል።
በዓድዋ የአልደፈር ባይነታችን ወኔና ፅናታችን በተግባር የታየበት ብቻም ሳይሆን ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን የደመቀበት ገድል መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
የዓድዋ ድል ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች ያስቆጣ፤ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በጋራ ለአንድ አላማ ያስተሳሰረና ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያዊነትን ያሳየ የጋራ የነፃነት ትግላችን ነው ብለዋል።
129ኛውን የዓድዋን ድል በዓል ስናከብር ኢትዮጵያውያን የጋራ አንድነታችንና የጀግንነታችን ማሳያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ክብርና የድል ፋና ወጊ በመሆኑ ለአባቶቻችን ተጋድሎ ታላቅ ክብር እየሰጠን መሆን ይገባል ነው ያሉት።