Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ እንቅስቃሴ 9 ነጥብ 7 ትሪሊየን ብር ደረሰ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ከ4 ዓመት በፊት ከ50 ቢሊየን ብር በታች የነበረው የዲጂታል ፋይናንስ የገንዘብ ዝውውር በአሁኑ ወቅት 9 ነጥብ 7 ትሪሊየን መድረሱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ግቡ ኢትዮጵያን ዲጅታል ማድረግ በመሆኑ የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በፋይናንስ እና በሌሎች ዘርፎች ዓላማውን ማሳካት ተችሏል ብለዋል፡፡

ከመታወቂያ አገልግሎት ጀምሮ የግብይት ሥርዓቱ በቴሌ ብር፣ በሞባይል ባንኪንክ እና በሌሎች አማራጮች በመከናወኑ የዲጂታል ግብይት የተለመደ ሆኗል ብለዋል፡፡

የፋይናንስ ስርዓቱን ጨምሮ በሁሉም ዘርፎች ኢትዮጵያን ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሚያሸጋግሩ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸው÷ በመንግሥት የኤሌክትሮኒክ ግዢ በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ የሚያደርግ የዲጂታል ስርዓት መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

“የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀድመን እየጨረስን ነው” ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው÷ በስትራቴጂው የተቀመጡ ቁልፍ መለኪያዎች ተሳክተዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ከአራት ዓመት በፊት ከ50 ቢሊየን ብር ብታች የነበረው የዲጂታል ፋይናንስ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት ወደ 9 ነጥብ 7 ትሪሊየን ብር መድረሱን ነው የገለጹት፡፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተመዘገቡ ስኬቶች ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተጀመረው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ መስመር እየያዘ መምጣቱን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል፡

በመሆኑም የተመዘገቡ ስኬቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እና የኢትዮጵያን ከዘመኑ የኢንዱስትሪ አብዮት ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የሚያሸጋግር የዲጂታል ስትራቴጂ በልጽጎ ገቢራዊ ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡

Exit mobile version