አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ91 ሺህ በላይ የብዝኃ ሕይወት ዝርያዎችን በመሰብሰብ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
በኢንስቲትዩቱ የአዝርዕትና ሆርቲ ካልቸር ምርምር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ውብሸት ተሾመ÷ የብዝኃ ሕይወት ሃብት በአግባቡ ጥበቃ ካልተደረገለት ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የብዝኃ ሕይወት ሃብት ላይ የተጋረጡ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ፈተናዎች መኖራቸውን ጠቁመው÷ እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም የተለያዩ ዝርያዎችን በመሰብሰብ የጥበቃ ሥራ እየተከናነወ ነው ብለዋል፡፡
እስካሁን ከ91 ሺህ በላይ ዝርያዎችን በመሰብሰብ የጥበቃ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ለዚህም በብሔራዊ ደረጃ ካለው ጅን ባንክ ባለፈ የመስክ ጥበቃ ቦታ መዘጋጀቱን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ገልጸዋል፡፡
በተያዘው ዓመት 650 ናሙናዎች ተሰብስበዋል ያሉት አቶ ውብሸት÷ በቀጣይ በዘርፉ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል፡፡
በተካልኝ ሀይሉ