Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ቀጣናውን የሚያስተሳስር ጥሪ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የቀጣናውን ሀገራት በኢኮኖሚ የሚያስተሳስር ጠቃሚ ጥሪ መሆኑን አሜሪካዊው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተመራማሪ ላውረንስ ፍሪማን (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

ተመራማሪው፤ የኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ ጥያቄ ፍትሐዊ መሆኑን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።

በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፤ ኢኮኖሚዋን ከዚህ በላይ ለማሳደግ የባሕር መዳረሻ እንደሚያስፈልጋት በአጽንኦት አንስተዋል፡፡

ለኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ በስምምነት መስጠት ማለት፤ የቀጣናውን ንግድ የሚያሳድግ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን የሚያነቃቃና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትም ይህንን ከግምት በማስገባት ኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ የምታገኝበትን አማራጭ ለማመቻቸት የምክክር ጠረጴዛ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡

ቀጣናው ከግጭት አዙሪት እንዳይወጣ የሚሠሩ አካላት፤ የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ አድርገው እያቀረቡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

ከሰሞኑ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የታዩ ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሂደቶች፤ የእነዚህ አካላት ፕሮፓጋንዳ የተሳሳተ ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሁለቱ ሀገራት ለጋራ ዕድገት በሚጠቅሟቸው ጉዳዮች ዙሪያ በመመካከር ላይ መሆናቸውን አውስተው፤ ይህም ኢትዮጵያ ቀጣናውን ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት አመላካች ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በቀጣናው ልዩነቶችን በንግግር መፍታት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡

በቃለአብ ግርማ

Exit mobile version