አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዜጎችና ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ምቹ ሁኔታ እንዲኖር እየተሠራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የፌዴራል እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ከወከላቸው ሕዝብ ጋር ያደረጉትን ውይይትና የመስክ ምልከታ አስመልክቶ ርዕሰ መሥተዳድሩ በተገኙበት ግብረ መልስ ተሰጥቷል።
በዚሁ ወቅትም በክልሉ የተረጋጋና ሰላማዊ የፖለቲካ አካባቢ በመፍጠር ለዜጎችና ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ምቹ ሁኔታዎች እንዲኖሩ እየተሠራ መሆኑን ርዕሰ መሥተዳድሩ አስረድተዋል፡፡
በተለይም የመንገድ፣ ድልድይ እንዲሁም ጤና እና የትምህርት ልማት ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በቀላሉ ወደ ሀብት መቀየር የሚያስችሉ የግብርና ሥራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንዲሁም በቱሪዝምና ማዕድን ምርት ላይ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ሥራዎችን እና ግንባታቸው የተጓተቱ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡
በጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦትን በማሳደግ የመድኃኒት ስርቆትን በመከላከል የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡