አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች እየተከበረ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ዕለቱ የሚከበረው “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ሐሳብ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬን (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በተገኙበት በሸገር ከተማ ኮዬ ፈጨ ክፍለ ከተማ ቀኑ በመከበር ላይ ነው፡፡
በተመሳሳይ የሴቶች ቀን በጋምቤላ ከተማ የተከበረ ሲሆን በዚሁ ወቅት በብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ምክትል ፕሬዚዳንት መስከረም አበበ እንዳሉት፤ ሴቶች በሀገር መሪነት፣ በዲፕሎማሲ፣ በግጭት አፈታት፣ በሰላም ግንባታ እና በመሳሰሉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
ባለፉት ዓመታትም የሴቶችን መብት ከማስጠበቅ፣ ፆታዊ ጥቃትን ከመከላከል እና ምላሽ ከመስጠት፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በውሳኔ ሰጭነት ከማብቃት አንፃር በተሠሩ ሥራዎች ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
እንዲሁም በትግራይ ክልል በመቐለ ከተማ በክልል ደረጃ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን እየተከበረ ነው፡፡
በአከባበሩ ላይ የፌደራል፣ የክልል እና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በተመሳሳይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እና ሌሎች የክልሉ አመራሮች በተገኙበት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሆሳዕና ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡
ቀኑን በማስመልከትም በሆሳዕና ከተማ የንግድ ባዛር፣ ኤግዚቢሽንና የፎቶ ግራፍ ዐውደ-ርዕይ መከፈቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡