Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የደሴ ከተማን የመጠጥ ውኃ ሽፋን ለማሻሻል ርብርብ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደሴ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን ለማሻሻል በሚደረገው ርብርብ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ፡፡

የደሴ ከተማን የመጠጥ ውኃ አቅርቦትና የፍሳሽ አወጋገድ ማሻሻል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ምክክር ተካሂዷል፡፡

የከተማዋ ውኃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ወርቁ አሞኘ በዚሁ ወቅት፥ የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋንን ለማሻሻል ከመንግሥት ዕቅዶች በተጨማሪ የከተማ አሥተዳደሩ፣ የነዋሪዎችና የባለ ድርሻ አካላት ርብርብ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የፋይናንስ ችግሮች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና በየጊዜው እየተሠሩ ካሉ መሰረተ ልማቶች ጋር ተያይዞ እያጋጠመ ያለውን የመጠጥ ውኃ እጥረት መቅረፍ የሚያስችሉ የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።

ጽሕፈት ቤቱ ያለበት የፋይናንስ ችግር ለደንበኞች የተሳለጠ አገልግሎት እንዳይሰጥእንቅፋት መሆኑን ጠቅሰው፤  የተፈጠረውን ችግር ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት ጥናቶች ተካሂደዋል ብለዋል፡፡

በቅርቡም አዲስ ታሪፍ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ክፍተቶቹ ይቀረፋሉ ማለታቸውን የቢሮው መረጃ አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል በከተማዋ በ652 ሚሊየን ብር ወጪ እየተከናወነ ያለውን የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት ግንባታ ጎብኝተዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም ግንባታውን በተያዘለት ለማጠናቀቅ፤ የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት የሥራ አመራር ቦርድ፣ የደንበኞች ፎረም እንዲሁም የከተማ አሥተዳደሩ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡

Exit mobile version