አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ31 ወርቅ አምራች እና በአንድ ወርቅ አቅራቢ በአጠቃላይ 32 ማህበራት ላይ ርምጃ መወሰዱን የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
ማህበራቱ ከ2016 በጀት ዓመት ጀምሮ ምንም አይነት ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ያላስገቡና የዕቅዳቸውን ከ10 በመቶ በታች አፈፃፀም ያሳዩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት ፍቃዳቸው ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ መደረጉን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ገብረ ማሪያም ሰጠኝ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ወርቅ በሚመረትባቸው ቦታዎች ተከታታይ ድጋፍ በማድረግ የወርቅ ምርት መጠንን ለማሳደግና ህገወጥ የወርቅ ምርት ዝውውርና ግብይትን በመቆጣጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ወርቅ ለማምረት ፍቃድ የወሰዱ አዳዲስ ማህበራት ፈጥነው ወደስራ እንዲገቡ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ተከትሎ የወርቅ ዋጋ መጨመሩን በመገንዘብ ህጋዊ መንገድ እንዲከተሉ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ የተቀመጠውን ወርቅ የማቅረብ ዕቅድ በማያሳኩና ዝቅተኛ አፈፃፀም በሚያሳዩ የወርቅ አምራች ማህበራት ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡