Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የደሴ ከተማን የኮሪደር ልማት በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ደሴ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ እድገትና ለሕዝቡ ተጠቃሚነት አዲስ ምዕራፍን የከፈተ መሆኑን የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ ከቧንቧ ውሃ – ሮቢት እየተገነባ የሚገኘው የአስፋልት ንጣፍ ሥራ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን÷ የኮሪደር ልማት ግንባታውን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለሕዝብ ጥቅም ለማዋል ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በኮሪደር ልማቱ የአካፋይ መንገድ፣ የመብራት ፖል ዝርጋታ፣ የካናል ሥራ፣ የውሃ መስመር ዝርጋታና ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

የኮሪደር ልማት የብስክሌትና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ ሌሎች መዝናኛ ሥፍራዎችን ያካተተ በመሆኑ ለጎብኚዎችና ለነዋሪዎች መዝናኛነት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለልማቱ ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው÷ እስካሁን ከ150 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version