አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ2017/18 ምርት ዘመን ከ150 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እና ከ45 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እንደሚሰራጭ ተገለጸ።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው እና ሌሎች አመራሮች በዳውሮ ዞን ኢሠራ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርትን ጎብኝተዋል።
አቶ ማስረሻ በላቸው በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ በየአካባቢው የሚገኙ ሀብቶችን በተገቢው በመጠቀም ምርታማነትን ለማጎልበት በትጋት እየተሰራ ነው።
በክልሉ ምርታማትን ለማጎልበት የሚያስችሉ ተፈጥሯዊ ሀብቶች እና አማራጮች እንዳሉ ተናግረዋል።
በተለይም የውሃ ሀብቶችን በተገቢው በመጠቀም እንደ ክልል ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸው፤ ለ2017/18 ምርት ዘመን ከ150 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እና ከ45 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ቀርቦ ስርጭት መጀመሩን ጠቁመዋል።
አርሶ አደሩ የጀመሯቸው የመስኖ ልማት ሥራዎች ይበልጥ እንዲስፋፉ የድጋፍና ክትትል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው፤ እንደ ዞን ከ 3 ሺህ ሄክታር የሚልቅ መሬት በመስኖ ለማልማት እንደሚቻል መለየቱን እና አሁን ላይ ወደ 16 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በበጋ ወራት ማልማት መቻሉን መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።