Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዘገባዎች የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ፍላጎት በመረዳት ሊሰሩ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የዓለምን ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስከብሩ ሥራዎች ላይ ይበልጥ አተኩረው እንዲሰሩ ተጠየቀ።

ተለዋዋጭ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ እና የጂኦ-ፖለቲካል አሰላለፍ በሚዲያ ሥራዎች የሚኖረው አንድምታ ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ተኮር የፓናል ውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

መድረኩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትና ሆርን ሪቪው ከተሰኘ ኦንላይን ሚዲያ ተቋም ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው።

ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተወጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉበት መድረኩ÷ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አሁናዊ የዓለም ተለዋዋጭ ዐውድ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ጨብጠው እንዲሰሩ ለማስቻል ያለመ ነው ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዲ ዘነበ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዲፕሎማት ዘሩባቤል ጌታቸው (ዶ/ር)ን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

አቶ በረከት ድሪባ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ጥቅም በማስከበር ረገድ ትልቅ የዲፕሎማሲ አቅምን ፈጥራሉ።

ለዚህም የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ፍላጎት መረዳት እንደሚገባ ጠቁመው÷ መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ፋይዳቸው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት በመስኩ የመገናኛ ብዙሃንን አቅም የሚያጎለብቱ ሥራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የዛሬው መድረክም መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥና ምክክር በማድረግ ግንዛቤን ለማስፋት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹምእሸት ሽመልስ በበኩላቸው÷ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የዓለምና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ግንዛቤ ይዘው ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና ፖለቲካ መስኮች የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት ማስቀደም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

Exit mobile version