Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የጎዴ መስኖ መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ምርታማነትን ጨምሯል ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በድጋሚ ታድሶ ባሳለፍነው ታኅሣስ ወር ወደ አገልግሎት የተመለሰው የጎዴ መስኖ መሰረተ ልማት ፕሮጀክት ለሶማሌ ክልል አዲስ የማምረት ዐቅም ሆኗል ተባለ፡፡

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አብዲዋሂድ ሙጀዲን እንደገለጹት፤ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ ታድሶ በድጋሚ አገልግሎት መስጠት በጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአካባቢውን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅትም በፕሮጀክቱ 4 ሺህ ሔክታር መሬት እየለማ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በቆሎ፣ ሩዝ፣ ስንዴ፣ ሀብሀብ፣ ማሽላ እና ሰሊጥ እየተመረተ መሆኑን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

በዚህ የመስኖ ፕሮጀክት 4 ሺህ አባዎራዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡

ከፊታችን ሚያዝያ ወር ጀምሮ የፕሮጀክቱን የማልማት ዐቅም በ3 ሺህ 620 ሔክታር ለማሳደግ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው፤ ይህም በኢንቨስተሮች የሚለማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የመስኖ ፕሮጀክቱ በአካባቢው የሚገኙ አርብቶ አደሮችን፤ ከፊል አርሶ አደር ከማድረግ ጀምሮ በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ከፍተኛ ዐቅም ሆኗል ብለዋል፡፡

ባለፈው ታሕሣስ ወር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው የጎዴ መስኖ መሰረተ ልማት ፕሮጀክት 27 ሺህ 600 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው እና ከ53 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የማድረግ ዐቅም አለው።

በቃለአብ ግርማ

Exit mobile version