አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴራል መንግሥት የላካቸውን 85 የእርሻ ትራክተሮች ዛሬ ለዞኖች ማስረከቡን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አሥተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ኢያሱ አብረሃ (ዶ/ር) በርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ በዘመናዊ የግብርና አሠራር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡
የእርሻ ሜካናይዜሽን ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀው፤ በክልሉ የአርሶ አደሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በእርሻ ትራክተሮቹ በኩታ ገጠም የተደራጁ አርሶ አደሮች እና ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ለተደረገው ድጋፍም ምሥጋና አቅርበዋል።
ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት እና ከአጋር አካላት የተገኙ 125 ትራክተሮች ተከፋፍለው ጥቅም ላይ መዋላቸውንም አውስተዋል፡፡

