አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)በኢትዮጵያ ለተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ የአስቻይነት ሚናውን በሚገባ ተወጥቷል ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ ገለጹ።
ዓለሙ ስሜ (ዶር) እና የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በተገኙበት የማክሮ ኢኮኖሚና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሂዷል።
ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፥ ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን አንስተዋል።
በቀጣይም ከዚህ የተሻለ እድገት እንደሚመዘገብ በርካታ አመላካች ሁኔታዎችች መኖራቸውን ነው የገለጹት።
ይህ አመርቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብም የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ የአስቻይነት ሚናውን በሚገባ መወጣቱን ተናግረዋል።
የወጪና ገቢ ምርትና የሀገር ውስጥ የጭነት እንቅስቃሴ በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ በዚሁ ልክ ራሱን ከማሳደግ በተጨማሪ እንደ አንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

