አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 30 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ 153 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠቱን አስታወቀ።
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይኸነው ዓለም ÷ በ2012 በጀት ዓመት ለ2 ሺህ 214 ባለሀብቶች ፍቃድ ለመስጠት ታቅዶ ለ2 ሺህ 908 ባለሀብቶች ፍቃድ መሠጠቱን ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከወሰዱት ባለሀብቶች ውስጥ 291 የሚሆኑት ወደ ስራ የገቡ መሆናቸውንም ነው የገለጹት ።
ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም 74 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
አቶ ይኸነው ዓለም አያይዘውም 47 ነጥብ 99 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባላሃብቶች ፍቃድ ለመስጠት ታቀዶ ÷153 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች ፍቃድ መሰጠቱን አስረድተዋል ።
ከስራ እድል አኳያም ለ228 ሺህ 42 ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ÷ ለ 395 ሺህ 804 ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል ።
ለክልሉ ኢንቨስትመንት መጨመር÷ የክልሉ ሰላምና ደህንነት ካለፉት አመታት የተሻለ መሆን፣ የህብረተሰቡ የመልማት ጥያቄ፣ የክልሉ ተወላጅ ባለሀብቶች የማልማት ፍላጎት ማደግ እንዲሁም የአመራሩ ቁርጠኝነት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
በናትናኤል ጥጋብ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

