አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 30 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል በድምቀት ይከበሩ የነበሩ የአደባባይ በዓላት የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሕዝብ በተሰበሰበበት እንደማይከበሩ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
በዓላቱ በተለየ መልኩ በችግኝ ተከላ እና በደም ልገሳ ስነ ስርዓቶች እንደሚከበሩ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኃይለኢየሱስ ፍላቴ አስታውቀዋል።
በየዓመቱ በክረምት በአማራ ክልል በደማቅ ሥነ ስርዓት የሚከበሩ ሀይማኖታዊ እና የሕዝብ በዓላት ከዚህ ቀደም ይከበሩበት ከነበረው በተለየ መልኩ እንደሚከበሩም ቢሮው አስታውቋል።
ነሐሴ 13 ቀን የሚከበረው ደብረ ታቦር (ቡሄ) በመላ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚከበር ቢሆንም በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር አካባቢ በተለየ ድምቀት መከበሩን አስታውሰው ÷ባለፉት ዓመታትም የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት ሲከበርም ቆይቷል ብለዋል።
ደብረ ታቦር ሀይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትውፊቱ ጎልቶ በተለይም በክርስትና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትርጉም ተሰጥቶት በየዓመቱ በድምቀት የሚከበር በዓል መሆኑን ጠቁመው ÷ከነሃሴ 15 እስከ 18 ቀን 2012 ዓ.ም በተመሳሳይ የሚከበሩት የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላትም በልጅ አገረዶች እና ወጣቶች በጉጉት የሚጠበቁ ናቸው ብለዋል።
የልጅ አገረዶች የነጻነት እና የወንዶች የማጌጫ በዓላት እንደሆኑ የሚነገርላቸው እነዚህ በዓላት በተለይም በሰቆጣ፣ በላል ይበላ እና በራያ ቆቦ አካባቢዎች በልዩ ልዩ ባሕላዊ ክዋኔዎች ይከበራሉ ነው ያሉት።
ከዚያም ባለፈ በክልል እና በሀገር ዓቀፍ ደረጃም በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ በርካታ ሕዝብ ተሰባስቦ በደመቀ ሁኔታ የሚከበሩ በዓላት መሆናቸውን አንስተዋል።
ተቀዛቅዞ የነበረውና በቅርቡ እየጎላ የመጣው ሌላው የአደባባይ በዓል ደግሞ የእንግጫ ነቀላና ከስኝ አጨዳ መሆኑን አንስተው ÷በዓሉ ከዘመን መለወጫ ጋር ተያይዞ ጳጉሜ እንደገባ በምስራቅ ጎጃም ዞን አካባቢ በልጅ አገረዶች እና በወጣቶች በጭፈራ፣ በሆታ እና ልዩ ልዩ ባሕላዊ ጨዋታዎች የሚከወን ትልቅ የአደባባይ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
እንደሌሎቹ የአደባባይ በዓላት ሁሉ በእንግጫ ነቀላ እና ከስኝ አጨዳም የተለያዩ የባሕል አምባሳደሮች እና ጎብኝዎች ይታደሙበታልም ነው ያሉት።
ከዚህ ቀደም በነበረው የበዓላት አከባበር የየበዓላቱን ባሕላዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ታሪካዊ ዳራ የሚያሳዩ አውደ ጥናቶች ፣ እያንዳንዳቸውን የሚወክሉ ትዕይንቶች እንዲሁም እንደየ ሁኔታው በዓላቱ እንዲደምቁ የሚያስችሉ ሁነቶች ሁሉ ይከወኑ እንደነበርም አስታውሰዋል ።
በተያዘው ዓመት ግን ለኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ሕዝብ በተሰበሰበበት እንደማይከበሩ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጠቁመው÷ከዚያ ይልቅ በተለየ መልኩ ችግኝ በመትከል እና ደም በመለገስ እንደሚከበሩ አስታውቀዋል።
ምናልባት ለወረርሽኙ በማያጋልጥ መልኩ ጥቂት ሰዎች
የሚታደሙበት አውደ ጥናት እና ኤግዚቢሽን ሊኖር እንደሚችልም ይጠበቃል ብለዋል።
የበሽታው ስርጭት ቀጣይነት የሚኖረው ከሆነ ግን በሌሎች ሕዝባዊ በዓላት ላይም ተመሳሳይ ውሳኔ ሊኖር እንደሚችል ኃላፊው መናገራቸውን የአብመድ ዘገባ ያመላክታል።።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

