Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጅቡቲ በህገወጥ መንገድ ለሚኖሩ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱበት ሰነድ ሊሰጥ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሀገሪቱ በህገወጥ መንገድ ለሚኖሩ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱበትን ሰነድ ሊሰጥ መሆኑን አስታወቀ።

የጅቡቲ መንግስት በህገወጥ መንገድ በሀገሪቷ ውስጥ በመኖር ላይ የሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች ለቀው አንዲወጡ መመሪያ ማስተላለፉ ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎ በጅቡቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዜጎች በፈቃደኝነት ተመዝግበው ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱበት ሰነድ መስጠት እንደሚጀምር በዛሬው ዕለት ባወጣው መረጃ አስታውቋል።

ኤምባሲው በመረጃው ላይ እንደገለጸው፤ ከሚያዝያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 24 ቀን ድረስ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር ግቢ ውስጥ ከጠዋቱ 4:00 ጀምሮ ምዝገባ ያካሂዳል።

በመሆኑም ዜጎች ለምዝገባ ወደ ስፍራው ሲመጡ ማንነታቸውን የሚገልጽ ሰነድ፣ የማህበራት ወይም የሀገር ቤት መታወቂያ ይዘው እንዲቀርቡ መጠየቁን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

አመልካቾቹ በቅርብ ጊዜ የተነሱትን ሁለት 3በ4 የሆነ ጉርድ ፎቶ ግራፍ እና የአገልግሎት ጊዜው ያለፈ ቢሆንም ፓስፖርት ይዘው እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።

Exit mobile version