Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኮምቦልቻ ከተማ በ736 ሚሊየን ብር ወጭ የተገነቡ ሁለት ፋብሪካዎች ስራ ጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ኮምቦልቻ ከተማ በ736 ሚሊየን ብር ወጭ የተገነቡ ሁለት ፋብሪካዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
ከ650 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት የሀድያ ዱቄትና የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ የብስኩት ፋብሪካ በቀን 16 ሰዓት በማምረት ላይ እንደሚገኝ የፋብሪካው ባለቤት አቶ ይመር አሊ ገልጸዋል።
ፋብሪካው ለ150 ሰዎች ቋሚና ከ100 በላይ ወጣቶች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸው፥ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ በምርትና በሥራ ዕድል ፈጠራ አበርክቶው የላቀ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ በከተማዋ ተመርቆ ስራ የጀመረው የድሪም ማካሮኒ እና ፓስታ ፋብሪካ ከ86 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበትና በቀን 144 ኩንታል የማምረት አቅም እንዳለው የፋብሪካው ባለቤት አቶ አደም መሐመድ ገልጸዋል፡፡
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሐመድ አሚን በዚሁ ወቅት፥ ፋብሪካዎቹ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ተኪ ምርቶችን እንደሚያመርቱ ገልጸው÷ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ በግንባታ ላይ ያሉ 110 የሚሆኑ ፋብሪካዎች ግንባታቸውን እንዲያፋጥኑ እየተሰራ ሲሆን፥ የከተማ አስተዳደሩ መሬት ወስደው ወደ ስራ የማይገቡ አልሚዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም ተገልጿል፡፡
በአለባቸው አባተ
Exit mobile version