Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በሲዳማ ክልል ምርት አቋርጠው የነበሩ 64 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሲዳማ ክልል ምርት አቋርጠው የነበሩ 64 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲመለሱ ማስቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

በንቅናቄው ኢንዱስትሪዎች የሚገጥሟቸው የመሰረተ ልማት፣ የፋይናንስ፣ የግብዓትና የሰው ኃይል አቅርቦት ችግሮች በመለየትና በመፍታት የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ማሳደግና ዘርፉ ለሀገር እድገት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ለማስቻል በትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች በንቅናቄው በተደረገው ክትትልና ትኩረት መጠናቀቃቸውን ጠቁመው÷ በዚህ ዓመት ብቻ 7 ኢንዱስትሪዎች ተመርቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አመላክተዋል።

ንቅውናቄው ማምረት አቋርጠው የነበሩ 64 ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውንና የኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅምም ከ44 ነጥብ 4 ወደ 59 ነጥብ 5 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ውጪ የሚላኩ የኢንዱስትሪ ምርትና የውጭ ምንዛሬ መጠን እንዲጨምር ማድረጉን እንዲሁም ተኪ ምርቶችን በጥራትና በአይነት በማምረት ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት ይወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሬ ማዳን ማስቻሉን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version