Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

መንግስት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያከናወነው የሪፎርም ሥራ ውጤት አስገኝቷል – አቶ አህመድ ሺዴ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ሰባት ዓመታት መንግስት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያከናወነው የሪፎርም ሥራ ውጤት ማስገኘቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ በ3ኛው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2017 የፓናል ውይይት ላይ እንዳሉት÷ የመንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይም አምራች ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን አድርጓል።

በአምራች ዘርፉ ከብድር አቅርቦት ጋር በተያያዘ የነበረው ከፍተኛ ችግር መፈታቱን ጠቁመው÷ ቀደም ሲል 85 በመቶ የባንክ ብድር ለመንገግስት የልማት ድርጅቶች የነበረውን አሁን ላይ ለአምራች ዘርፉ እየተሰጠ መሆኑን አመላክተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መስፋፋት እና መሳለጥ ተግዳሮት የነበሩ ጉዳዮችን በወሰደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መፍታት መቻሉን አንስተዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከተደረገባቸው ዘርፎች አንዱ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ነው ያሉት ሚኒስትሯ÷ በዚህም በመጀመሪያውና በ2ኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የዘርፉን ችግሮች በመፍታት አምራች ዘርፉ ላይ ለውጥ እንዲመጣ መደረጉን ተናግረዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በ10 ዓመቱ የልማት እቅዶች የተቀመጡ ኢላማዎችን ለማሳካት ትልቅ እገዛ ማድረጉን ገልጸዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ÷ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በአሁኑ ወቅት በመሰረታዊ ሁኔታ እየተፈታ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ከአምናው ዘንድሮ ለአምራች ዘርፉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን እና አሁን ላይ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ከውጭ ጥሬ እቃ ለማስገባት የውጭ ምንዛሪን እንደ ችግር ማንሳቱ ቀንሷል ብለዋል።

አጠቃላይ ሪፎርሙ የብድር፣ የውጭ ምንዛሪ፣ የሃይል አቅርቦትንና የገበያ እንዲሁም የሎጂስቲክስ ችግሮችን የፈታ ነው ብለዋል።

በታሪኩ ለገሰ

Exit mobile version