አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በተደጋጋሚ በሚያስተላልፉት መልዕክት ‘ኢትዮጵያ የምታክብረው የድል ቀን እንጂ የነጻነት ቀን አይደለም’ ይላሉ።
ይህ የነጻነት ቀን በነጻ የተገኘ ሳይሆን ቀደምት አባቶች በከፈሉት የላብ፣ የደም እና የአጥንት ዋጋ ነው።
የአርበኞች ድል መታሰቢያ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን የሚገልጹት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ ፋሺስት ጣሊያን በዓድዋ ጦርነት የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ሲል ከ40 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገው ሙከራ ከጀግኖች አርበኞች መስዋዕትነት እንደሆነ ይናገራሉ።
በወቅቱ የነበሩ ጀግኖች አባቶች በአርበኝነት ታግለው የሀገርን ነጻነት በመጠበቅ ለዚህ ትውልድ አስተላልፈዋል።
ይህ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከነጻነት ቀን ይልቅ የድል ቀን በማክበር ላይ ትገኛለች።
ለዚህ የድል ቀን ያበቃን የአባቶች አርበኝነት በመሆኑ ትውልዱም የአርበኝነት መንፈስ በመውረስ ለመጪው ትውልድ የጸናች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማስረከብ ይጠበቅበታል።
በየዓመቱ ሚያዚያ 27 የሚከበረውን የአርበኞች ድል መታሰቢያ ስናከብር እኛም መጪው ትውልድ ይዘክረን ዘንድ አሻራ አኑረን ማለፍ እንዳለብን ብዙዎች ይስማሙበታል።
የዚህ ዘመን ትውልድ አርበኝነት ዘመኑን የዋጀ መሆን የሚጠበቅበት ሲሆን፤ በተለይም ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማረጋገጥ የብልጽግና ጎዳና ላይ የሚያራምድ መሆን አለበት።
ስለሆነም ሁሉም በተሰማራበት መስክ ውጤታማ ለመሆን ነገን በማሰብ መትጋት ይኖርበታል።
ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት ከታሪክ ስብራት ለመውጣት የተጀመሩ ስራዎች አሉ። በተለይም ከትርክት ጋር በተያያዘ የነጠላ ትርክት የኢትዮጵያን የወደፊት ጉዞ በማደናቀፍ ላይ የሚገኝ መሆኑ ግንዛቤ በማግኘቱ ይህንን የማረም ስራ ተጀምሯል።
የነጠላ ትርክት ዋጋ እንዳያስከፍለን በአሁኑ ወቅት በስፋት እየተሰራበት ያለው የወል/የጋራ ትርክት የተሻለው አማራጭ መንገድ ነው። የኢትዮጵያን አዎንታዊ ትናንት ለጋራ እሴት ግንባታ በማዋል ለነገ ትውልድ ሀገርን ማስረከብ ወሳኝነት አለው።
ለዚህ ደግሞ ዛሬ ያለው ትውልድ የኢትዮጵያን ጸጋዎች አውቆ የተደመረ ሀብት መፍጠር የሚጠበቅበት በመሆኑን የሀገሪቱን ባህላዊ እሴት፣ ቋንቋ፣ እምነት፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ወዘተ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታ ማዋል ያስፈልጋል።
ሌላው የትውልዱ አርበኝነት ሊሆን የሚገባው ከድህነት የተላቀቀች እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለቀጣይ ትውልድ ማስረከብ ነው። በዚህ ረገድ በለውጡ ዓመታት ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት በተደረገው ትግል ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየት ጀምረዋል።
ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን እየተሻገረች በአሁኑ ወቅት የማንሰራራት ዘመን ላይ ደርሳለች።
ለዚህም በኢኮኖሚው መስክ የተደረጉ ማሻሻያዎች የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው ሲሆን ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተነደፉ ኢኒሼቲቮችም ውጤታማ መሆን ጀምረዋል።
በአረንጓዴ አሻራ፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄዎች የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ፣ በኢንፎርሜሽን ደህንነት እና በፈጠራ ዘመኑን የዋጀ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በሚኪያስ አየለ