አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከ128 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የወልዲያ አረዳ መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክት ተመርቋል።
ፕሮጀክቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በይፋ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
የመስኖ ፕሮጀክቱ የአርሶ አደሮችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማሳደግና ገበያ በማረጋጋት ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑ ተገልጿል።
2 ሺህ 850 ሜትር ዋና ካናል እና 3 ሺህ 100 ሜትር መለስተኛ ካናል በድምሩ 5 ሺህ 950 ሜትር ርዝመት ያለው የካናል ግንባታ እና 5 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መያዝ የሚችል የገንዳ ሥራ እንደተሰራም ተመላክቷል።
በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት 120 ሜትር ርዝመት ያለው በሶዶ ወረዳ የሻሾ ወንዝ ተንጠልጣይ ድልድይ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
ድልድዩ ከ7 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት የተገለጸ ሲሆን÷ ለሰዎችና ለእንስሳት አገልግሎት ምቹ እንዲሆን ተደርጎ የተገነባ መሆኑም ተገልጿል።
በኦሊያድ በዳኔ