Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከ10 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ እየተከፋፈለ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ10 ሚሊየን 729 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮሙኒኬሽን እና ማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራ አመራር ሥራ አስኪያጅ ጋሻው አይችሉህም ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ 600 ሺህ ኩንታል ዳፕ የአፈር ማዳበሪያ ትናንት ጂቡቲ ወደብ ደርሷል፡፡

ተቋማቸው ለ2017/18 የምርት ዘመን ከውጭ እየገዛ ከሚገኘው 24 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስከ ዛሬ ወደብ የደረሰው የማዳበሪያ መጠን ከ11 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል በላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ 10 ሚሊየን 729 ሺህ 522 ኩንታል ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ በኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካይነት ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተከፋፈለ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

 

በሌላ በኩል 73 ሺህ ኩንታል ዩሪያና 550 ሺህ ኩንታል ዳፕ ግንቦት 1 እና 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርሱ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

በዮሐንስ ደርበው

Exit mobile version