አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በቀል እውቀቶችን በመመዝገብ በህግ አግባብ ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
ሀገር በቀል ዕውቀቶችን እና የቱሪዝም አቅምን ለዘላቂ ልማት ለመጠቀም የሚያስችል የምክክር መድረክ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ወልዱ ይመስል÷ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማህበረሰብ ዕውቀትን በሚገባ መጠቀም አለመቻሏን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የማይዳሰሱ እና የማይጨበጡ በርካታ የማህበረሰብ ዕውቀት ሀብት ቢኖሯትም በአዕምሯዊ ንብረት ባለመመዝገባቸው በተገቢው መንገድ ዕውቅና ማግኘት እና መልማት አለመቻላቸውን ገልፀዋል፡፡
በዚህም ባለስልጣኑ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማስመዝገብና በህግ እንዲጠበቁ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊ ምሁራን በበኩላቸው÷ ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለቱሪዝም ዘርፍ እንዲውሉ እና የሥራ ዕድል እንደፈጥሩ ለማስቻል በጥናትና ምርምር የተደገፉ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ሀገር በቀል ዕውቀት እና ቱሪዝም ላይ ትኩረት ያደረጉ 13 ጥናታዊ ጽሁፎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
በቲያ ኑሬ