አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳደግ የአዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ፣ የነባሮች ማሻሻያና ማስፋፊያ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 23 አውሮፕላን ማረፊያዎች መደበኛ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም 22 የአነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያዎች በባለስልጣኑ እውቅና አግኝተው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በፌደራል መንግስት አምስት ኤርፖርቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ ነባሮቹ ላይም የማስፋፊያና የማሻሻያ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋት፣ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍላጎት አንጻር ያለው መሰረተ ልማት በቂ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ይህን በመገንዘብም የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ባለስልጣኑ ከፌዴራል መንግስት በተጨማሪ የክልል መንግስታት፣ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ባለሀብቶች ኤርፖርት እንዲገነቡ እና እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱን ጠቁመዋል፡፡
ይህን ተከትሎም 32 አዳዲስ አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ለመገንባት ጥያቄ መቅረቡን ገልጸው፤ ባለስልጣኑ ቦታው ድረስ በመሄድ መረጣ ማካሄዱን አስገንዝበዋል።