አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ቀጣና መገኘት ለአካባቢው ሰላም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው የቀድሞ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባል ፔቲ ኦፊሰር ወንድወሰን አሰፋ ገለጹ፡፡
ፔቲ ኦፊሰር ወንድወሰን ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አንድ እድል ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ጥያቄ በተመለከተ ምልከታቸውን አጋርተዋል፡፡
የቀድሞ ባሕር ኃይል በነበረው የ35 ዓመታት ቆይታ፤ በቀይ ባሕር በኩል በኢትዮጵያ ላይ አንድም የውጭ ወራሪ ጥቃት እንዳልቃጣ አውስተዋል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ለጸጥታና ደኅንነት ወሳኝ መሆኑን ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በቀይ ባሕር ቀጣና በመንቀሳቀስ ሰላም ስታስከብር መቆየቷንም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ በባሕር ክልሉ መገኘት ከራሷም አልፎ ለአካባቢው ሰላምና ደኅንነት የሚኖረው ጥቅም የሚያጠያይቅ አለመሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር በማጣቷ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም፣ ለሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች መዋል የሚችለውን ከፍተኛ ሀብት ለወደብ ክፍያ እያዋለች መሆኗን አንስተዋል፡፡
ይህን ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት ብሎም የቀጣናውን ደኅንነት ጭምር ለመጠበቅ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ በዲፕሎማሲና በሰጥቶ መቀበል መርህ መንቀሳቀስ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
በመንግሥት እየተደረገ ከሚገኘው ጥረት ባሻገር ዜጎች በሀገር ፍቅር ስሜት የባሕር በር ጥያቄውን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበው፤ በተለይም የወጣቶችን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ከራሷ ባሻገር ለጎረቤት ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን የማስገንዘብ ሥራ በስፋት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡
ፔቲ ኦፊሰር ወንድወሰን አሰፋ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይልን በ1973 ዓ.ም የተቀላቀሉ ሲሆን፤ ተቋሙ እስከፈረሰበት ጊዜ ድረስ ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡
በተጨማሪም በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ በተለያዩ ኩባንያዎች መርከበኛ በመሆን ሠርተዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ