አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና ኬንያ የንግድ ስምምነትን ወደ ተግባር ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሁለቱ ሀገራት የተቀላጠፈ የጠረፍ ንግድ ማዕቀፍ ላይ በሦስት ዙር ያደረጉትን ድርድር በመቋጨት ባለፈው ወር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
ስምምነቱ በድንበር አካባቢ የሚገኙ ዜጎች ከመሃል ሀገር በቀላሉ ማግኘት የማይችሏቸውን ምርቶች በጠረፍ ንግድ እንዲያገኙ ለማስቻል ያለመ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወንድሙ ፍላቴ ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፥ በስምምነቱ መሰረት የጠረፍ ንግዱ ከኢትዮጵያ ድንበር በ50 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከኬንያ ድንበር በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ያሉ አካባቢዎችን ይሸፍናል፡፡
በጠረፍ አካባቢ ንግዱ የሚቀርቡ ምርቶችን በተመለከተ የገበያ ፍላጎትና ለአካባቢው ማህበረሰብ አስፈላጊ የተባሉ ምርቶችን በጥናት በመለየት በስምምነቱ መካተቱን ገልጸዋል፡፡
ከቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ አዝዕርት፣ የምግብ ዘይት፣ መጠጦች፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ አልባሳትና ጫማዎች፣ የቤት መገልገያና የመዋቢያ ቁሳቁሶች ውጪ ሌሎች ምርቶችን መገበያየት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡
ስምምነቱ የምርት አቅርቦት እንዲሳለጥ፣ ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል፣ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
የንግድ ስምምነቱን ወደ ትግበራ ለማስገባት የጠረፍ ንግድ አሰራር መመሪያን ከማዘጋጀት ጀምሮ የንግድ ፍቃድ መስጠትን የመሳሰሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ነው አቶ ወንድሙ የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ እንዲሳለጥ ምርቶች ከህግ አግባብ ውጭ ከሀገር እንዳይወጡ የጠረፍ አካባቢ ማህበረሰብ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ