አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኩርዱ ታጣቂ ቡድን (ፒኬኬ) ከአራት አስርት ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ወደ ሰላማዊ ትግል ለመምጣት መወሰኑን አስታወቀ፡፡
ቡድኑ ውሳኔውን ያስተላለፈው በፈረንጆቹ 2025 ከግንቦት 5 እስከ 7 ባደረገው ኮንግረስ ነው።
ፒኬኬ ለ40 ዓመታት ያደረገው የትጥቅ ትግል የኩርዲስታንን ህዝብ ለከፋ ችግር ዳርጎታል ያለው ቡድኑ÷የኩርድን ጥያቄ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መፍታት የተሻለ አማራጭ ሆኖ መገኘቱን ገልጿል፡፡
በ12ኛው የቡድኑ ኮንግረስ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የቡድኑ ወታደራዊ መዋቅሮች እንደሚፈርሱ የገለጸው ቡድኑ÷ ከዚህ በኋላ በቡድኑ ስም የሚደረግ ማንኛውም አይነት ወታደራዊ ዘመቻ አይኖርም ብሏል፡፡
የቱርኩ ኤኬ ፓርቲ ቃል አቀባይ ኦማር ቼሊክ÷ፒኬኬ ሰላማዊ አማራጭን መቀበሉ ከሽብር ስጋት ነፃ የሆነች ቱርክን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡
ቡድኑ ያሳለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ካደረገ እንዲሁም ሁሉንም የፒኬኬ ክንፎች ካፈረሰ እና ህገ ወጥ መዋቅሮችን ከዘጋ ቱርክ ከቡድኑ ጋር ንግግር ማድረግ እንደምትጀምር ማረጋገጣቸውን አናዶሎ ዘግቧል፡፡
በሚኪያስ አየለ