Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሪፎርሙ ዓላማ ተወዳዳሪ ምኅዳር መፍጠር ነው – አቶ ማሞ ምኅረቱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የተገበረችው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ዋና ዓላማ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹና ተወዳዳሪ ምኅዳር መፍጠር መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ አስገነዘቡ፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 የቢዝነስ ፎረም ላይ አቶ ማሞ እንዳሉት፤ የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ዓላማ ኢንቨስትመንትን መደገፍ እንዲሁም ተወዳዳሪ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምኅዳርን መፍጠር ነው።

ይህም በውስጡ በርካታ ፕሮግራሞችን መያዙን ገልጸው፤ የፕሮግራሙ ዋናው አካልም የገንዘብ ፖሊሲን ከማዘመን ጋር የተያያዘ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሪፎርሙ ተግዳሮቶችን በተሻለ ሁኔታ መፍታት የሚያስችል ሆኖ መዘጋጀቱንና ኢንቨስተሮችንም ገቢ ማመንጨት የሚያስችላቸው ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ግዙፍ የታዳሽ ኃይል ባለቤት መሆኗን አንስተው፤ በቀጣናው ቁልፍ ተዋናይ ሆና መቀጠሏን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት መንግስት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ዘላቂ እድገት ለማምጣት ወሳኝ እርምጃዎችን መውሰዱንም ጠቅሰዋል፡፡

በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ እድሎችን ማስፋትን የሚያካትቱ ቁልፍ ተግባራት መከናወናቸውንም ነው ያነሱት፡፡

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአብዛኛው ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆኖ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የፍትሕ ሚኒስትር ሀና አርዓያሥላሴ  ናቸው፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት ወሳኝ እርምጃ መወሰዱን አውስተው፤ በተሻሻለው የኢንቨስትመንት ሕግም በርካታ ዘርፎች ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡

Exit mobile version