አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ2 ሚሊየን ብር በላይ በህይወት ከሌለ ደንበኛ ሂሳብ ወደ ሌላ ሂሳብ በማስተላለፍ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ የባንክ ሰራተኛን ጨምሮ ሰባት ግለሰቦች በጽኑ እስራት እና በገንዘብ እንዲቀጡ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ከፍተኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት ወሰነ።
ተከሳሾቹ 1ኛ ግርማዬ ተሾመ፣ 2ኛ ምስክር ግርማ፣ 3ኛ ታሪኩ በሬሳ ጨምሮ ሰባት ናቸው።
በ1ኛ ክስ በ1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) (ሀ)፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 (1) (ሀ) እና (2) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ዝርዝር ክስ ቀርቦባቸዋል።
1ኛ ተከሳሽ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ አ.ማ ቦምብ ተራ ቅርንጫፍ ኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ ሆኖ ሲስራ የማይገባ ጥቅም ለራሱ ለማግኘት ወይም ለ2ኛ እና 3ኛ ተከሳሶች ለማስገኘት በማሰብ የባንኩ ቢርቢርሳ ቅርንጫፍ ደንበኛ ከነበሩት በህይወት ከሌሉት የግል ተበዳይ አቶ ገነነ ተሾመ ወርቁ ሂሳብ ቁጥር ባለቤት ባልቀረቡበት ወይም ትዕዛዝ ባልሰጡበት ሁኔታ ካለደንበኛው ፍቃድ በማከናወን ለ3ኛ ተከሳሽ 1 ሚሊየን 172 ሺህ ዝውውር በማጽደቅ እንዲሁም በተመሳሳይ ቀን ለ2ኛ ተከሳሽ 830 ሺህ ዝውውር በማጽደቅ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሶች በሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም ገቢ ተደርጎላቸዋል።
1ኛ ተከሳሽ በስራ ሃላፊነቱና በስራ መዘርዝሩ ምክንያት ዝውውሮችን እንዲያጸድቅና ትክክለኛነታቸውን እንዲያረጋግጥ የተሰጠውን ሃላፊነት እንዲሁም የባንኩ የደንበኞች ሂሳብ እና ኦኘሬሽን መመርያ አንቀጽ 9.2.4 የጣለበትን የቀረቡ ከሂሳብ ወደ ሂሳብ ገንዘብ ይዘዋወርልኝ ጥያቄዎችን ትክክለኛነት እና የሰነዱን ሙሉነት በማረጋገጥ የማጽደቅ ሃላፊነቱን ወደ ጎን በመተው ከደንበኛ ትዕዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ከደንበኛው ሂሳብ የገንዘብ ዝውውር እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ በመስጠት እና የገንዘብ ዝውውሩን በማጽደቅ ለ2ኛ እና 3ኛ ተከሳሽ እንዲከፈል ያደረጉ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና እና ልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በስልጣን አላግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በ2ኛ ክስ ደግሞ ሁሉም ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀፅ 32 (1) (ሀ)፣ የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 33 እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 (1) (ሀ) (ለ) እና (ሐ) ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል።
በዚህም ተከሳሾች ገንዘቡ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸው ከላይ በ1ኛ ክስ ላይ በተጠቀሰው የሙስና ወንጀል የተገኘውን የአቶ ገነነ ተሾመ ሀብት የሆነውን ሕጋዊ አስመስለው በማቅረብ የገንዘቡን ምንጭ በመደበቅ ያለአግባብ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾችን ተጠቃሚ በማድረግ ወደ እያንዳንዳቸው ሂሳብ ገቢ በማድረግ የገንዘቡን ሕገ ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን ወይም ወንጀል የፈጸመውን ሰው ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ለማድረግ ገንዘቡን የለወጡ ወይም ያስተላለፉ በመሆኑ እና ገንዘቡን የተረከቡ ወይም የተጠቀሙ በመሆኑ በፈጸሙት በሙስና ወንጀል የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በዚህም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት 1ኛ ተከሳሽ በ4 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት እና 5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ፣ 2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ 5ኛ፣ 6ኛ እና 7ኛ ተከሶሾች በሌሉበት በ11 ዓመት ከ3 ወር ፅኑ እስራት እና 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተወስኖባቸዋል፡፡
5ኛ ተከሳሽ በዋስትና ከተለቀቀ በኋላ ፍርድ ቤት መቅረብ ባለመቻሉ 225 ሺህ ብር እንዲቀጣ ችሎቱ ወስኗል።
በሲፈን መኮንን