አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቻይና እና ብራዚል የሩሲያ-ዩክሬን የሰላም ንግግርን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን የሰላም ንግግር በመጪው ሐሙስ በቱርክ ኢስታንቡል ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የብራዚሉ አቻቸው ሉላ ዳ ሲልቫ በቤጂንግ ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት የሩሲያ-ዩክሬን የሰላም ንግግርን እንደሚደግፉ መግለጻቸውን የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማዖ ኒንግ ገልጸዋል፡፡
መሪዎቹ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላም ለማስፈን የሚያስችል ንግግር ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ሙሉ የሚደግፉ መሆናቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ካለፈው እሁድ ጀምሮ በቻይና ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ለምታደርገው የሰላም ንግግር ዝግጅቷን መቀጠሏን ማረጋገጣቸውን የዘገበው አናዶሉ ነው፡፡
ከትናንት በስቲያ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር በቀጥታ ለመወያየት ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗን መግለጻቸው ይታወሳል።
በአቤል ንዋይ