Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል የተቀናጀ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ፣ ሥርዓተ ምግብና፣ የእናቶችና ሕጻናት ጤና አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሄደ።

በ42 ወረዳዎች እና በ8 ከተማ መሥተዳድሮች ለሚገኙ ከ332 ሺህ በላይ ሕጻናት ተደራሽ ለማድረግ የታለመ ዘመቻ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን ሀቢብ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ የፌስቱላ ምርመራ፣ የቫይታሚን ኤ ሥርጭት እንዲሁም የእናቶች እና ሕጻናትን የአመጋገብ ሥርዓት ለማስተካከል የሚያስችሉ ተግባራት ከክትባቱ ጎን ለጎን እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ ከተማ በባቦጋያ ጤና ጣቢያ በይፋ የተጀመረው የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ መጀመሩን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የተቀናጀ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻው ከአምስት ዓመት በታች ክትባት ላልጀመሩና ጀምረው ላቋረጡ ሕጻነት እየተሰጠ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የተቀናጀ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ለተከታታይ 10 ቀናት በሁሉም ክልሎች ይሰጣል ብሏል፡፡

በዚህም ከ17 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሕጻናትን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱ ተገልጿል፡፡

የክትባት ዘመቻው ዋና ዓላማም የእናቶች እና ሕጻናትን ሞት መቀስ ሲሆን፤ የዘመቻው ግብ እንዲሳካ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲረባረቡ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በከሊፋ ከድር

Exit mobile version