Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በቅንጅት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አበባ ታመነ ለፋና ዲጂታል እንደገለፁት÷ በዘርፉ የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት ወደ ተግባር ተገብቷል።

መንግስት ተግባራዊ ያደረገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ወሳኝ የኢኮኖሚ ምሰሶ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአምራች ዘርፉ እንደ ግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ሌሎች ዘርፎችን እንዲደግፍ ለማድረግ በርካታ ንቅናቄዎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አንዱ መሆኑን በአብነት አንስተዋል።

ንቅናቄው ኢትዮጵያ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ማምረት እንደምትችል ያሳየችበት እንደሆነ ተናግረዋል።

በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት የሰለጠነ የሰው ሀይል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሀይል ለመፍጠር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የሰለጠነ የሰው ሀይል አንዱ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አካል መሆኑን በመግለጽ፤ በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የዘርፉ ተማሪዎች በተለያዩ ኩባንያዎች የተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በአምራች ኢንዱስትሪ ላይ በችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች ላይ የሚሳተፉበት እድል መመቻቸቱን ጠቁመዋል።

በሚኪያስ አየለ

Exit mobile version