Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ምርታማነትን እያሳደገ ነው – ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ምርታማነትን በማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ቴክኖሎጂው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለዓመታዊ ጥቅል ምርት እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለአብነትም በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የምርት መጠንን በማሳደግና ጥራትን በማሻሻል ተወዳዳሪ ለመሆን ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በግብርና ዘርፍ የግብዓት አጠቃቀምን ለማዘመንና የአየር ሁኔታን አስቀድሞ ለመተንበይ ቴክኖሎጂው የፈጠረው እድል ምርታማነትን ለማሳደግ አስችሏል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ባለፈም የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ በማቀላጠፍ የዜጎችን እንግልት ለማስቀረት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዘርፉን ጥቅም አስቀድማ በመረዳት ፖሊሲ በመቅረጽና ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ እንዲሁም ተቋም በመገንባት ውጤታማ ሥራ እያከናወነች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በአንጻሩ ቴክኖሎጂው በሀሰተኛ መረጃ ሥርጭት በአሉታዊ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ገልጸው፥ ችግሩን ለመከላከልም የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ሀገራዊ እድገቱን ለማገዝ ከትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተከታታይ እያስተናገደቻቸው በሚገኙ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ መድረኮች የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አቅምን ለማሳደግ የሚያግዙ ልምዶች እየተገኙ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

በሃይለማርያም ተገኝ

Exit mobile version