አዲስ አበባ፣ ግንቦት 7፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ሰላም ማስከበር ተጨማሪ ወታደራዊና የፖሊስ ኃይል በማሰማራት ድጋፍ እንደምታደርግ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) አረጋገጡ፡፡
በሚኒስትሯ የተመራ የልዑካን ቡድን በጀርመን በርሊን ለሁለት ቀናት በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተሳትፏል።
በስብሰባው ማጠቃለያ ዕለት በስብሰባው ንግግር ያደረጉት አይሻ መሀመድ (ኢ/ር)፥ ድርጅቱ በሚያቀርበው ጥያቄ መሠረት ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወታደራዊና የፖሊስ ዩኒቶችን ለሰላም ማስከበር ተግባር እንደምታሰማራ ቃል ገብተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባቋቋመቸው ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር የስልጠና ኢንስቲትዩት አማካኝነት በስልጠና ላይ የምታደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
በተለይም ኢንስቲትዩቱ በሴት ሰላም አስከባሪዎች ስልጠና ላይ በቀጣይነት በትኩረት እንደሚሰራ መግለጻቸውን የመከላከያ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኮሙኒኬሽን አማካሪ ወ/ሮ ስመኝ ግዛው ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
በኃይለማርያም ተገኝ