አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኪነ ጥበብ ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ለተጀመረው ጥረት አይነተኛ ሚና ይጫወታል ሲሉ የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) ገለጹ፡፡
ሚኒስትር ዴዔታው ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ኪነ ጥበብ በሁሉም ሀገር ውስጥ አካባቢን ባሕልን፣ ትውፊትን፣ ቋንቋ እና ታሪክን እንዲሁም ማህበራዊ መስተጋብርን የመግለጽ አቅም አለው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥም ኪነ ጥበብ ያለፈውን እና የወደፊት መዳረሻን ለመሰነድ በማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሀገርን ለመሳል ጥቅም ላይ ሲውል መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የነበሩ ጥበበኞች የኢትዮጵያን መልክ ሲገልጹ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው÷ጥበብ በኢትዮጵያ በሚቀያየሩ መንግስታት ታሪክ የራሱን አሻራ ጥሎ ማለፉን ገልፀዋል፡፡
ከዓድዋ ጦርነት በኋላ ጥበብ ጥኩረት ተሰጥቶት እንዲስፋፋ መድረጉን ጠቅሰው÷በተለይም እንደ ቴአትር እና ኪነት አይነት የኪነ ጥበብ ቡድኖች መመስረታቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህም በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት አርበኞች ጣልያንን እንዲመክቱ ጥበብ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ በተለይም በለውጡ መንግስት ለጥበብ እና ጥበበኞች ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ሚኒስትር ዴዔታው አስገንዝበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ1 ሺህ 500 በላይ ከሚሆኑ ከያንያን ጋር ምክክር ማድረጋቸው ለትኩረቱ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
የከያንያንን ጥያቄዎች መሰረት በማድረግ መንግስት የክዋኔና የእይታ ጥበባት ትምህርቶችን በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረጉን እንዲሁም የቴአትር፣ የሙዚቃ ማቅረቢያና የትወና ቦታዎችን መገንባት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
“ኪነ ጥበብና ሀገር፣ ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የውይይት መድረክ እየተካሄደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
መርሐ ግብሩ የኪነ ጥበብ ሰዎች በሀገር ልማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች የሚገኙ የጥበብ ሰዎች በመሳተፍ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሃሳብ እንዲያንጸባርቁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ