አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9 ፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መልካም እሴቶችን ለመገንባትና ለማጽናት ከኃይማኖት ተቋማት ባሻገር ሁሉም በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መጋቤ ይታገሱ ኃይለሚካኤል አስገነዘቡ።
ሶስተኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባዔ ግንቦት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡
ጉባዔውን ተከትሎ መጋቤ ይታገሱ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት÷መልካም እሴቶችን በማሕበረሰቡ ውስጥ ለመገንባት በአንድ ተቋም ብቻ የሚቻል አይደለም።
በተለይም የኃይማኖት ተቋማት የጋራ በሆኑ እሴቶች ላይ ጠንከር ያሉና ተከታታይነት ያላቸው ትምህርቶችን መስጠት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ አንዳንድ እሴቶቻችንን የሚሸረሽሩ መልዕክቶችን ለመታገል ኃይማኖታዊና ሀገራዊ እሴቶችን ቀድሞ በማድረስ መታገል እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡
የኃይማኖት ተቋማት ከመንፈሳዊ ተልዕኳቸው በተጨማሪ በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራ ፈጠራ፣ በሙያ ስልጠና እንዲሁም በሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ተግባር ላይ በስፋት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ግጭትን በመፍታት፣ አብሮነትን በማጽናት፣ ሰላምን በመገንባት እና በማስረጽ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የኃይማኖት ተቋማት ዕሴቶቻቸውን ከማጉላት አንፃርና የሚሰሯቸውን ሥራዎች ለሕብረተሰቡ በማድረስ ረገድ የሚዲያዎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በትብብር መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሶስተኛውን ዓለም አቀፍ የሰላም የአብሮነትና የልማት ጉባዔ በኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ህብረት፣ በአፍሪካ ህብረት፣ በቡድን -20 ኢንተርፌይዝ ፎረምና ዩናይትድ ሪሊጂየስ ኢኒሼቲቭ በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ