አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ዕዝ ባለፋት ወራት በሶደሬ ጊዜያዊ ማሰልጠኛ ያሰለጠናቸውን መሰረታዊ ወታደሮች አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የደቡብ ዕዝ ም/አዛዥ ሜጀር ጄነራል አድማሱ አለምነህን ጨምሮ ሌሎች የዕዙ ከፍተኛ መኮንኖችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ተመራቂዎቹ የአካል ብቃት፣ የተኩስ እና ልዩ ልዩ የሥነ ልቦና እና ወታደራዊ ስልጠናዎች በስኬት ያጠናቀቁ መሆናቸው ተገልጿል።
በደቡብ ዕዝ የ202ኛ ኮር አዛዥ ኮሎኔል ደጀኔ ጸጋዬ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ሀገር ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ዘመኑን የዋጀ ብቁ ሰራዊት መገንባት ያስፈልጋል።
ተመራቂዎች አስፈላጊውን ወታደራዊ ሳይንስና ተለዋዋጭ የጠላትን ስትራቴጂያዊ ስልት መገንዘብ የሚያስችል ሥልጠና መውሰዳቸውን አንስተዋል።
የሀገርን ሉዓላዊነትና ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ በሥነ ልቦና የታነጸ እና ግዳጁን በጥብቅ ዲሲፒሊን የሚፈጽም ሠራዊት የመገንባቱ ሒደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
የታሪካዊ ጠላቶችን ተልዕኮ በመቀበል ኢትዮጵያን የግጭት ማዕከል ለማድረግ የሚሰሩ አካላትን ለመደምሰስ ዕዙ ዝግጁ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ደቡብ ዕዝ የውጭና የሀገር ውስጥ ግጭት ጠማቂዎችን ከመመከት ባለፈ ሕገ ወጥ ኮንትሮባንድን ለመከላከል በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
ተመራቂዎቹ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሚገባ በመወጣት ሀገራቸውን እንዲጠብቁም አሳስበዋል።
በመላኩ ገድፍ